የኢኮኖሚያችንን ምንጭ ዘግተን፤ የድህነትን በር በመክፈት የምናሸንፈው ጠላት አይኖርም – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት

ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) የኢኮኖሚያችንን ምንጭ ዘግተን፤ የድህነትን በር በመክፈት የምናሸንፈው ጠላት አይኖርም ሲል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የመግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

የአማራ ሕዝብ በረጅም ዘመናት ታሪኩ በደራሽ ሁነቶች ተጠላፊ ሳይሆን ነገን ዓላሚ፤ አርቆ አሳቤ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ ነው። ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ጋር በመቻቻል፣ በአብሮነትና በአንድነት መኖርን ቀዳሚ ምርጫው ያደረገ ሕዝብ ነው።

የእኩልነት፣ የፍትሃዊነት እንዲሁም የመብትና የጥቅም ጥያቄዎቹ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱለት ይሻል። ምክኒያቱም ከሰላም እንጂ ከጦርነትና ከግጭቶች የሚያተርፍና ያተረፈ ሕዝብና ሀገር የለም፡፡ የግጭቶች ሁሉ መጨረሻ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት፣ ድህነትና ጉስቁልና ነው።

በተለይም ክልላችን በጦርነት የቆየ፤ በነበረው ጦርነቱም ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች የደረሱበት ነው፤ ጦርነቱ በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል። በዚህ ምክንያት በስነልቦና የተጎዳው ህዝባችን እና የወደመው ሃብትና ንብረት ገና በተገቢው መንገድ ማገገም አልቻለም። ህዝባችን አስተባብረን ያልተቋረጠ የመልሶ ግንባታ ስራ መስራት ይጠይቀናል።

ይሄን ለማድረግ የክልላችን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ ብቼኛው የምርጫ ጉዳይ ይሆናል። ሰላም በሌለበት የምናሳካው የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት አይኖርም። እንደ ሕዝብ በጦርነት ባጅተን በጦርነት መዝለቅን ብቼኛ አማራጭ ማድረግ አስፈላጊም ተገቢም አይደለም። በጦርነትና ግጭት የተጎሳቆለ እንጅ የተገነባ አገር፤ የተቀየረ ሕዝብ የለም።

ከትርክት ነቃሽነት እና ትናንትን ወቃሽነት ይልቅ ከትናንታችን በሚገባ በመማር ለነገ የተሻለውን መምረጥ አስፈላጊ ነው። ልዩነት አይቀሬና ተፈጥሯዊ ነው። ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ ማስተናገድ ደግሞ የስልጣኔና የዘመናዊነት መገለጫ ነው። የሚያጋጥሙ ክልላዊም ሆነ አገራዊ ችግሮች ሁሉ በንግግር መፍታትን ባህል ማድረግ ይኖርብናል።

በዓለማችን ላይ አደጉ የሚባሉ ሀገራት በፈተናዎች ውስጥ አልፈው የዳበረ ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉትና ኃያላን ለመባል የበቁት የሃሳብ የበላይነትን መርህ ማድረግ በመቻላቸው ነው። በአንጻሩ ልዩነቶቻቸውን በሃሳብ ትግል ከመፍታት ይልቅ የጠመንጃ አፈሙዝን ምርጫ ያደረጉ ሀገራት ደግሞ በአደባባይ ሲበታተኑና ኢኮኖሚያቸው ደቅቆ ሲጎሳቆሉ አይተናል። ታሪክም ያስረዳናል።

አሁናዊ ክልላዊ ሁኔታችንም ከዚህ ትምህርት እንድንወስድ ያስገድደናል፤ ፖለቲካዊም ሆነ ሕዝባዊ ስክነት እና አስተውሎትን ይጠይቃል። በመካከላችን ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጥላቻና መለያየትን ምርጫ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል።

ምክንያቱም በደቦ ፍርጃና እርስ በርስ በመገዳደል ጥቁር ጠባሳን እንጅ ለህዝብ የሚጠቅም ደማቅ ታሪክ ማኖር አይታሰብም። መሪን በመግደልም መሪ መሆንም ሆነ መሪ ማውጣት አይቻልም። የአማራ ሕዝብ  በመከባበርና መቻቻልን ባሕል አድርጎ የዘለቀ እንጅ መገዳደል ታሪኩም አይደለም። እንዲህ አይነት ተግባር ለማንም የማይጠቅም እኩይ ዓላማ በመሆኑ በአንድ ድምጽ መወገዝ አለበት።

በሌላ በኩል በብዙ ቢሊዮን ወጪ የተገነቡ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መንገዶች ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገናኙ፤ ንግድንና ማሕበራዊ ግንኙነትን የሚያሳልጡ ናቸው። በተጨማሪም ሕሙማንን ተንቀሳቅሰው ሕክምና የሚያገኙበት፣ ጥረው ግረው የሚያድሩ ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚያፈሩበት ጭምር ነው።

ይሁን እንጅ  እነዚህን መንገዶችን መዝጋት፤ ትራንስፖርት ማስተጓጎል፤ ሱቆችንና የህዝብ  አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ስራቸውን እንዳይሰሩ ማድረግና የስራ ማቆም አድማ መጥራት ተጨማሪ ክልላዊ ኪሳራ እንጅ ትርፍ አይኖረውም። የለውም፤ሊኖረውም አይችልም።

ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከማድረስ ውጭ የሚያስገኘው የግለሰብ፣ የቡድንና የሕዝብ ዘላቂ ጥቅም የለም፡፡ ለሕዝብም ሆነ ለሀገር አይበጅም። የአማራን ሕዝብ የኢኮኖሚ ማሳለጫ መንገድ ዘግተን፤ የድህነት በር በተከታታይ በመክፈት የምናረጋግጠው ልማትና ስኬት እንዲሁም የምናሸንፈው ጠላትም አይኖርም።

አንዲህ አይነት ተግባሮች ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ለውጥ ከሚፈልግ አካል የሚመነጩ ባለመሆናቸው ለቀናት ይቅርና ለደቂቃዎች የሚስተጓጎል ክልላዊ ማህበራዊ መስተጋብር መኖር የለበትም በሚል የጸና አቋም መያዝ የሁሉም ሕዝብ ድርሻ ነው።

የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅሞች፣ የእኩልነት የፍትሃዊነት ጥያቄዎች ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል። ክልላዊም ሆነ አገራዊ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት መፈታት አለባቸው ብሎ ያምናል። ይህንን አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል።

ስለሆነም በአንድነትና በትብብር የድህነትና የመጠፋፋት፤ ሴራና ተንኮልን ዘግተን የልማትና የእድገት ጎዳናዎችን ክፍት ማድረግ አለብን። ምክንያቱም ለደቂቃዎች የሚስተጓጎል የሕዝባችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትና የሚከሰት ግጭት አሁናዊ የክልላችን ኢኮኖሚ የሚወስን ብቻ ሳይሆን የወደፊት ህልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን መረዳት ይገባል።