በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አተገባበር ላይ ማሻሻያ ተደረገ

ታኅሣሥ 5/2014 (ዋልታ) በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አተገባበር መመሪያ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እስካሁን ሲተገበር በቆየው መመሪያ ላይ ማሻሻያ ማድረግ በማስፈለጉ በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠም ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ መወሰኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች  ከሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ የማስገጠምና በተቀመጠው ደረጃ መሰረት መገጠሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ነበረባቸው፡፡

ይሁንና በአተገባበሩ ላይ እየታየ ያለውን ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፈተሸ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት ተጠናቆ ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ ማሻሻያ ተደርጓል ብሏል፡፡

የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያው ሊገጠምባቸው የሚገባቸው ተሽከርካሪዎች ዓይነትና ተያያዥ ችግሮችን በጥናት በመለየት ምላሽ መስጠት በማስፈለጉ በፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ አተገባበር ላይ ማሻሻያ መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

ስለሆነም አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ባለንብረቶች በማንኛውም ጊዜ መግጠም እንዳለባቸው አውቀው፤ የግዴታ ስምምነቱን እየፈረሙና አስፈላጊ ሰነዶቻቸውን በአባሪነት በማያያዝ በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠም ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡