ሚያዝያ 29/2014 (ዋልታ) በታንዛኒያ በሕገ-ወጥ መልኩ በመግባት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ 4 ሺሕ 500 ኢትዮጵያዊያን በምሕረት እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡
ስምምነቱ የተደረሰው በዳር ኤስ ሰላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ቀዲዳ በዛሬው ዕለት በታንዛኒያ የሚግሬሽን ኮሚሽን በመገኘት ከኢሚግሬሽን ኮሚሽነሩ አና ፒ ማካካላ (ዶ/ር) እና የታንዛኒያ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ኮሚሽነር ሳምዌል ማሂራኔ ጋር በመገናኘት ሰፊ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።
አምባሳደር ሽብሩ ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ካቀረቡ በኋላ በታንዛኒያ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ከማሳደግ አንጻርም የታንዛኒያ መንግሥት በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ ታንዛኒያ በመግባት ወንጀል ተከስሰው በእስር ላይ ላሉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ምሕረት እንዲያደርግ እና ከእስር እንዲፈታ ጥያቄ አቅርበዋል።
ኮሚሽነሮቹ በበኩላቸው አምባሳደሩ ያነሱትን የምሕረት ጥያቄ በተመለከተ በአጠቃላይ በታንዛኒያ በእስር ላይ ለሚገኙት ዜጎች የታንዛኒያ መንግሥት በሙሉ ምሕረት የሚያደርግ መሆኑን እና ሁሉም ከእስር ተፈትተው ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በቀጣይ የምሕረት ሂደቱ የአገሪቱን ሕግ በተከተለ መልኩ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ የሚፀድ መሆኑን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።