የቻይና እና ህንድ ወታደሮች በድንበር ጉዳይ ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸውንና ከሁለቱም ወገን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መደረሱ ተነገረ፡፡
ግጭቱ ከሶስት ቀናት በፊት የህንድ ግዛት በሆነችው በስኪሚ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ናኩላ አካባቢ የተከሰተ ሲሆን፣ ውጥረቱም እየተባባሰ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
አሁን የተጋጩበት ድንበር 3ሺህ 440 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2020 ሰኔ ወር ላይ በአካባቢው የድንበር ግጭት ተነስቶ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
በግጭቱም ጋላዋን ሸለቆ አካባቢ 20 የሚሆኑ የህንድ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ በወቅቱ ውጥረቱን አባብሶት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ህንድና ቻይና ከዓለም ረዥም የሚባሉ ድንበሮችን የሚጋሩ ሀገራት ሲሆኑ፣ በህዝብ ብዛት ቁጥርም ቢሆን ከዓለም ቀዳሚዎቹና የሰፋፊ ግዛቶች ባለቤት ናቸው፡፡
በዓለም ረዥም ከሚባሉ ድንበሮች አንዱና መልከአ ምድሩ በተራራ፣ በሀይቆችና በጠመዝማዛ ኮረብታዎች የተሞላው የሀገራቱ አዋሳኝ ድንበር ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ ሁልጊዜ የግጭት መንስኤ መሆኑ ይነገራል፡፡
ሀገራቱ በዘመናቸው ሁለት ጊዜ ብቻ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ እሱም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1962 እንደሆነና በወቅቱ ህንድ በጦርነቱ ተሸንፋ ከባድ ጊዜን ማሳለፏን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡