በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀረ- ሠላም ሀይሎች እንቅስቃሴና መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሰት የተሰጠ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁሉን አካታች የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሁም ብዝሃ ክፍለ ኢኮኖሚ በመገንባት ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሠላምና የልማት ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ በፖለቲካው መስክም የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር የሚያስችሉ ልምምዶችን ተግባራዊ በማድረግ ቅቡልነት ያለውን ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

ከእነዚህም አንኳር ተግባራት ውስጥ አንዱ ገለልተኛና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር የመከላከያ ሠራዊት በመገንባት በሀገራችን ላይ ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣውን ጥቃት መከላከል ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን እየተስተዋለ ያለው ይህንን የሀገር ሉዓላዊነት አስከባሪ ኃይል የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት የጥቂት ወገኖች ጥቅም አስከባሪ አድርጎ በመሳል የተለያዩ ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ጫናዎች ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ይስተዋላል፡፡

ስለሆነም የመከላከያ ሠራዊታችንን መንካትና ማጠልሸት ሉዓላዊነታችንን መዳፈር በመሆኑ ሁላችንም የአንድነታችን ዓርማ ከሆነው የሀገር ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፍ ይኖርብናል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመብትና የጥቅም ጥያቄዎች አብሮነትንና አንድነትን በማይሸረሽሩ እንዲሁም በጋራ ማደግና መበልጸግ እሴት ላይ በመመሥረት ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መብትና ጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ በሰከነ መንገድ በመነጋገር የጋራ መፍትሔ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡

የክልሉ ሕዝብ ካለፈው የጦርነት ጉዳት ሳይወጣና በዚህ የክረምት ወቅት አርሶ አደሩ እርሻ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት በሌላ ተደራራቢ ችግር ውስጥ ሲገባ በጣም ያሳዝናል፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮችን በሰከነ መንገድ በመነጋገርና በመመካከር እንዲሁም በህግ አግባብ በማስደገፍ መፍታት አለብን እንጂ በትጥቅ ትግል ለመመለስ መሞከር ውጤት አልባ ነው፡፡ ከጦርነት ሠላም አናተርፍም፡፡ ከትናንቱ የጦርነት ወቅት ጠባሳ ሙሉ በሙሉ ሳናገግም ለሌላ ጦርነት መንደርደር የለብንም፡፡

የክልላችን ሕዝብና መንግሥት በሁሉም ማዕዘናት ሠላም ሲኖር በክልላችን ውስጥም ሠላም ይሰፍናል የሚል ሙሉ እምነት አለው፡፡

በሀገራችን ላይ ሠላምን ለማስፈን በሚደረገው ምክክሮችና ውይይቶች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበርክት መሆኑን እየገለጽን የአማራ ክልል ህዝብን ለማሰቃየት በተለያዩ መንገድ ነፍጥ አንግቦ የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎችን ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጋር በመሆን የምንታገላቸው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡