በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ዜጎች ባዘጋጁት ቴሌቶን ከ12 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን
ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ዜጎች ባዘጋጁት ቴሌቶን 12 ሺህ 425 የአሜሪካ ዶላር መሰብሰቡ ተገለጸ።
“የሶስት ሺህ ለጋሾች አሻራ ቴሌቶን” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው መርሃ ግብር በበይነ መረብ አማካኝነት ትናንት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ ዋና ፀሐፊ አቶ ደምለው አልማው የተሰበሰበውና ቃል የተገባው ገንዘብ በመጠለያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ብርድ ልብስ በመግዛት ድጋፍ እንደሚደረግ ለኢዜአ ገልጸዋል።
12 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሰላም ጓድ የልዑካን ቡድን ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣና የ14 ቀናት ቆይታ ለማድረግ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።