በአንድ ቀን ብቻ 67 ሰንጋዎችን የበለተው በሬ አራጅ


ታኅሣሥ 28/2015 (ዋልታ) ኤፍሬም ደምሴ ህይወቱ ሙሉ ከእርድ ጋር የተቆራኘ ሲሆን በአዲስ አበባ ቄራዎች ላለፉት 26 ዓመታት እርድ በመፈፀም ሙያ ላይ የተሰማራ ሰራተኛ ነው፡፡

በስራ ላይ ባሳለፈባቸው ዓመታት አንድ ኪሎ ስጋ ከ 15 ብር ተነስቶ እንደየደረጃው እስከ 1 ሺሕ 500 ብር ሲሸጥ በአራጅነት ሙያው ላይ ሆኖ ታዝቧል፡፡

በህይወት ውጣ ውረድ በዘመናት መለዋወጥ ዑደቶች ዞረው በሚመጡ አውደ አመቶች የእርድ ስራን በማቀላጠፍ አቶ ኤፍሬም የበርካታ የአዲስ አበባ ቄራ ደንበኞችን ቤት አድምቋል፡፡

በሬ ከማረድ ባለፍ ለስጋ ግድ የለኝም የሚሉት አቶ ኤፍሬም ሽሮ እና አትክልት መመገብ የዘወትር ምርጫዬ ነው ሲሉ የስጋ አምሮቴን የምወጣው በአይን ብቻ ነው ይላሉ፡፡

በተለይ እንዲ በአመት በዓል ወቅት ስጋ ንክች አላደርግም የሚሉት አቶ ኤፍሬም የቄራው ሰራተኞች በበዓል ሰሞን በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ ስለሚቆዩ በእለቱ ትልቁ እርካታቸው የእንቅልፍ ሰዓት ማግኘት ነው፡፡

ሁሌም በአውዳመት አባዛኛውን ሰዓታቸውን ከፍተኛ ጫና ባላው ስራ ላይ ስለሚያሳልፉ የተቀረውን ጥቂት ሰዓት ደግሞ በእንቅልፍ እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ፡፡

ኤፍሬም ደምሴ በአዲስ አበባ በቄራዎች ድርጅት ውስጥ አንጋፋ ከሚባሉ ሰራተኞች ውስጥ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን የድርጅቱ ሰራተኛ ከሆነበት እለት አንስቶ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያገለገለ ታታሪ ሰራተኛ ናቸው ፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ከ26 ዓመት በፊት እሳቸው ሥራ ሲጅምሩ እና አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያነፃፅሩ ለውጡ የሰማይና የምድር ነው ሲሉ አሁን ድርጅቱ ሥራን የሚያቀላጥፉ በርካታ ማሺኖች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡

ወትሮም አንድ ሰንጋ ይታረድበት የነበረው ሰዓት እና ጉልበት አሁን አስር ሰንጋ ለማረድ ያስችላል ይለሉ የአዲስ አበባ ቄራዎች አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያነፃፅሩ፡፡

በቀን ከ25 እስከ 30 ሰንጋ በአማካይ የሚበልቱት አቶ ኤፍሬም የበዓል ሰሞን ግን ይህ ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምር ይናገራሉ፡፡

በአንድ የኩዳዴ ቅበላ በዓል ወቅት የበለቱትን የሰንጋ ቁጥር ዞር ብለው ሲያስቡት ለእሳቸውም ይገርማቸዋል፡፡

በእለቱ 67 ሰንጋዎችን እየበለቱ አጥንት እየከሰከሱ ብልት በማውጣት ደንበኞቻቸውን በትጋት ያገለገለበትን ቀንን መቼም አይረሱትም፡፡

አቶ ኤፍሬም በ26 አመታት የሥራ ዘመኑ ውስጥ አልፎ አልፎ ከሚያገጥመው የእጅ መቆረጥ ውጪ የከፋ አደጋ ገጥሞትም አያውቅም፡፡ ነገር ግን በአንድ ወቅት በህይወታቸው የማይረሱት አንድ መጥፎ አጋጣሚ በጓደኛቸው ላይ እንደተከሰተ ይናገራሉ፡፡

በዚህም አንድ በሬ ከአራጆች አምልጦ የጓደኛቸውን እግር የቀነጠሰበትን አጋጣሚ በህይወቱ ከማይረሳቸው አሳዛኝ አጋጣሚዎች መካክል የማይረሳው ክስተት ነው ብለዋል ፡፡

መጪውን የገና በዓል አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያን ሰላም ያርግልን ለመላው የአዲስ አበባ ቄራ ድርጅት ባለደረቦቼና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፡፡

በሬ በማቅረብና በተለያዩ መንገዶች ስራቸውን እያቀላጠፉላቸው ለሚገኙ ለቄራና አካባቢው ወጣቶችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሳሙኤል ሙሉጌታ