በአዲስ አበባ በዘጠኝ ወራት በተከሰቱ አደጋዎች 670 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ


ሚያዝያ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ አበባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከሰቱ አደጋዎች 670 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማ አስተዳደሩ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባና አካባቢዋ 392 አደጋዎች አጋጥመው 670 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ ከ11.5 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል።

በደረሱት አደጋዎች 39 ሰዎችን ከእሳት አደጋ 85 ሰዎች ደግሞ ከሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ማትረፍ ችለናል ብለዋል።

በሌላ በኩል በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ሰዎች በእሳት አደጋ ህይወታቸው ሲያልፍ በኮንስትራክሽን አደጋ፣ ተቆፍሮ ክፍቱን በተተውና ውሃ ባቆሩ ጉድጓድች የሰው ህይወት ማለፉም ተገልጿል።

በ41 የመኖሪያ ቤት እና 35 የንግድ ቤቶች ላይ የእሳት አደጋ መድረሱም ተመላክቷል።

በዘጠኝ ወራት የደረሱ አደጋዎች ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የንብረት ወድመት መጠን በ37 ሚሊየን ብር የቀነሰ ሲሆን የአደጋ ቁጥር በ4 መጨመሩን ባለሙያው ገልጸዋል።

በአድማሱ አራጋው