በአዲስ አበባ የተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ፖሊስ

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው የሕወሓት ጁንታ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም፣ ለመከላከያ ሰራዊታችን እና ለሌሎች የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ ለተሰማሩ የፀጥታ አካላት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለፅ እና የሰራዊታችን ደጀን መሆናቸውን ለማሳየት እንዲሁም 2ኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሰላም መጠናቀቅን በማስመልከት ዛሬ ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ ያደረጉት ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል።

መርሐ-ግብሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ተግባራቸውን ማከናወናቸውን በመጥቀስ በዚህ ስራ ላይ ለተሳተፉ እና ሃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ የፀጥታ አካላት እንዲሁም ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች በፍፁም ጨዋነት፣ በትዕግስት እና በተባባሪነት መንፈስ የፀጥታ አካሉን በመደገፋቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡