በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም መደገፍ አለበት ተባለ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ አሁን ካጋጠሟት ችግሮች ተላቃ ዘላቂ ሰላምና የህዝብ አንድነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ሁሉም መደገፍ አለበት ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔን (ርክበ ካህናት) በከፈቱበት ጊዜ እንደገለጹት ሕዝቡን በማስተማርና በመምከር ወደ ዕርቅና ይቅርታ ማምጣት ይገባል ብለዋል።

ይህም ተግባር የኃይማኖት አባቶች ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

አገራዊም ሆነ ኃይማኖታዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ሕዝብን በኃላፊነት የሚመሩት ዓለማውያንም ሆኑ ኃይማኖታዉያን ለሠላም መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኃይማኖታውያን ለችግሩ ራሳቸውን የመፍትሔ አካልና የሠላም ጠበቆች መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

“በአገሪቱ የሚታየው ራስን ማብለጥና ሌላውን ማንጓጠጥ አርመን በፍቅር ለመለወጥ ካልጣርን የሕዝቡን መከራ ማሳጠር አንችልም” ያሉት ብጹእነታቸው፤ ሰላምንና አንድነትን ለማረጋገጥ ጉልበትን እንደ አማራጭ መውሰድ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የተከሰቱትን ችግሮች በውይይትና በድርድር ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ በመስጠት በጦርነትና በድርቅ እየተጎዱ ያሉ ወገኖችን መታደግ እንደሚገባ

አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በቤተ-ክርስቲያን፣ በቤተ-ክርስቲያኗ አገልጋዮችና በምዕመኑ ላይ ይደርሳሉ ያሏቸው ጉዳቶች እየበረቱ መምጣታቸውን ገልጸው፤ ይህም ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሥርዓተ-አምልኮ ከሚካሄድባቸው አደባባዮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ውዝግቦችን ለማስቀረት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጉባኤው በሰላም፣ በዕርቅና ይቅርታ ዙሪያ በስፋት ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል ብለዋል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ።