በኦሮሚያ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት አስመዝግበዋል – ሽመልስ አብዲሳ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

መስከረም 20/2016 (አዲስ አበባ) በኦሮሚያ ክልል የህብረተሰብቡን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባለፉት ሁለት ቀናት በጅማ እና አካባቢው ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በዋናነት በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት፣ እንዲሁም የግብርና ስራዎችን ተመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ የመደመር ዕሳቤን ማዕከል በማድረግ አራት መሰረታዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት፣ ወደ ውጭ የሚላክን ምርት ማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራን ማሻሻል መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቀመጡ ኢንሼቲቮችን መነሻ በማድረግ በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም በክልሉ በመኸር እና መስኖ የሚለማውን የመሬት ሽፋን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ በዋናነት የህዝብ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ክልል ተሞክሮ በመውሰድ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የሩዝ ምርትም ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ በሩዝ ምርት ራስን ከማቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመረውን ስራ በማገዝ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ያረጁ የቡና ዛፎችን በአዲስ በመተካትና በአዲስ መልክ የቡና ችግኞችን በመትከል ረገድ አበረታች ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ከ5 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን መትከል መቻሉን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ የቡና ምርትን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የምርት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የወጭ ንግድን ማሳደግ ላይ ያተኮሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በመኸርና በጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሰሩ ስራዎች ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዥ ታወጣው የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት ባለፈ ተጨማሪ ምንዛሪ ማስገኘት ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ ከፍተኛ የመልማት አቅም መኖሩን ገልጸው ይህንን አቅም በቴክኖሎጂ በማገዝ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን መናገራውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህንን የአርሶ አደሩን ትጋት በአግባቡ በመደገፍ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ የላቀ ውጤት እንደሚረጋገጥም ነው የተናገሩት።

በጅማ ዞን የተመዘገበው ስኬትም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡