በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

በኦሮሚያ  ክልል የተለያዩ ከተሞች መንግስት እያከናወነው ላለው የለውጥ ተግባርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አስተዳደር ድጋፍ ለመስጠት ዛሬም ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

በትናንትናው ዕለት በክልሉ በርካታ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።

ዛሬ እየተደረገ ባለው የድጋፍ ሰልፍ ህብረተሰቡ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የለውጥ ተግባር የሚያደንቁ ሃሳቦች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።

ሰልፈኞች ይዘዋቸው በወጡና እያሰሟቸው ባለው የድጋፍ ድምጾች የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስትና ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አስተዳደር ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

ሰልፈኞቹ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ለተመዘገበው ውጤት ዕውቅና ሰጥተዋል።

ከምርጫ ውጪ በጉልበትና በሀይል ስልጣን ለማግኘትና ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ ቡድኖችን አውግዘዋል።

ባሰሟቸው መፈክሮችም ‘የኦሮሞ ህዝብ የአጥፊዎች ዋሻ አይደለም’፣ ብለዋል።

“ጀግኖችን ማወደስና ማክበር የኦሮሙማ እሴት ነው፤ በጁንታው መቃብር ላይ ብልፅግና፥ ሰላምና የህዝቦች አንድነት ይለመልማል፤ የተጀመሩ የህግ የበላይነት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ፤ የኦነግ ሸኔን አጥፊ ተግባር እናወግዛለን” የሚሉ መፎክሮች ተስተጋብተዋል።

አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚያሴሩ ሃይሎችን በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
(ምንጭ፡- ኢዜአ)