በክልሉ ከመኸር እርሻ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ

መኸር እርሻ

ጥር 1/2015 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከመኸር እርሻ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አሸናፊ ክንፉ በ2014/15 የመኸር እርሻ ወቅት በክልሉ 303 ሺሕ 776 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን እና እስካሁን ከ246 ሺሕ 252 ሄክታር መሬት በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከተሰበሰበው ምርት አንፃር 65 ነጥብ 6 በመቶ እንደሆነና ከሄክታር አንፃር ደግሞ 81 ነጥብ 1 በመቶ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ምርቱ የተጠበቀውን ያህል እንዳይገኝ በዘር ወቅት የቴክኖሎጂ እና አፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር መስተዋሉንም እንደ ችግር አንስተዋል፡፡

በዘር ወቅት 64 ሺሕ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ መሸፈን እንደተቻለ የጠቀሱት ኃላፊው ይህም በስንዴ፣ ባቄላ፣ አቴር፣ ጠፍ፣ ጥራጥሬ እና ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች መሸፈኑን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ሀገር ለስንዴ ምርት በተሰጠው ትኩረት በክልሉ በመኸር ወቅት 23 ሺሕ 763 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ መሸፈኑን የጠቆሙት ኃላፊው በዚህም ከ16 ሺሕ 898 ሄክታር መሬት 535 ሺሕ 667 ኩንታል የስንዴ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ደጋማ አካባቢዎች አሁንም የሰብል ምርቶች እየተሰበሰበ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው