በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሀገር አቀፍ የተደራጀ መረጃ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ


መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሀገር አቀፍ የተደራጀ መረጃ እንደሚያስፈልግ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋሙ ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር ሀገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ ለማሰባሰብና ለማደራጀት የዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የሚደራጁ የአምራች ኢንዱስትሪ መረጃዎች መንግስት ለዘርፉ የሚያቀርበው መሠረተ ልማቶችና የማበረታቻ ሥርዓቶችን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ እንደ ሀገር ያሉንን ፀጋዎች ለመጠቀምና የሃብት ብክነትን በመቀነስ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የመረጃ ክፍተትን የሚሞላ እንሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም ለግብዓት አቅራቢዎች ታማኝ መረጃ ለመስጠትና በኢንዱስትሪዎች መካከል የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሀገሪቱን ብልፅግና የምናረጋግጠው ታማኝ የሆነና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ለፖሊሲዎችና ለውሳኔዎች አጋዥ እንዲሆኑ ማድረግ ሲቻል በመሆኑ ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡