በደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚያስተባብር ግብርኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የሰላም ሚኒስቴር በደቡብ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚያስተባብርና የሚመራ ግብርኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ግብርኃይሉ በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ በመገኘት በአካባቢው እርቅ እንዲፈጸምና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተዘጋጀው እቅድ ላይ ከወረዳው አመራሮች ጋር በመወያየት መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡

የወረዳው አመራር በራሱ አቅም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በተለያየ አካባቢ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ በማሰባሰብ በወረዳው በቼ በልቻኖ ቀበሌ ውስጥ ለ31 አባወራ እና እማወራ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደተጀመረ ግብርኃይሉ ማረጋገጥ እንደቻለ ተገልጿል፡፡

በቀጣይም ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለሚመለሱ ተፈናቃዮች ቦታ የመምረጥ ስራ የሚያከናውን ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ እየገባ እንደሆነ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡