አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተመራ ልዑክ የኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሃመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ እንዲሁም ከምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሱልጣን ቢን ሰዓድ አልሙሬይኪ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በኳታር ዶሃ የሥራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የልዑክ ቡድኑ በኳታር ከሚገኙ የተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ኳታር ግንኙነት እና ከኳታር ባለስልጣናት ጋር ስለተደረገው ውይይት፣ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ውስጣዊ ችግሮች እና የውጭ ጫናዎች መቋቋም እንድትችል እና ወደተሻለ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ሁሉም ዜጋ በሚኖርበት አገር ሆኖ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አምባሳደሩ አሳስበዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ፈታኝ ሁኔታ በድል መውጣት እንድትችል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ እና ዓለም አቀፉን ጫና በመቋቋም ለአገራቸው አለኝታነታቸውን እንዲያሳዩ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።