መስከረም 6/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ ለዓለም የማስረዳትና የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ድርጊት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየትን ዓላማ ያደረገው “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ -መንግስት” የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ በጋምቤላ ክልል በይፋ ተጀምሯል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ዘመቻውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ዘመቻው የኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም በተለይም ለምዕራባውያን መንግስታት ለማሳወቅና ለማስረዳት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት ሌት ከቀን ከፍተኛ ዘመቻ እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ዘመቻው የጁንታውን ሴራ ለማክሸፍና ተጨባጭ እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ለማሳየትና የውጭ ጫናን ለመመከት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሯች ጎች በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ ህልውና ላይ የተነሳውን ጠላት ለመደምሰስና የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም መንግስት እያደረገ ካለው መጠነ ሰፊ ጥረት በተጨማሪ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡
በክልሉ ከ50 ሺሕ በላይ ወጣቶች “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” የንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ እንደሚሳተፉ ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡