ባለፉት ሰባት ቀናት ናሙና ከሰጡ ግለሰቦች መካከል 13% ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

የካቲት 18፣ 2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ከየካቲት 11 እስከ የካቲት 17 ድረስ ባሉ ቀናት ናሙና ከሰጡ ግለሰቦች መካከል 13 በመቶዎቹ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ባለፉት 7 ቀናት 47 ሺህ 204 ናሙና ከሰጡት ግለሰቦች ውስጥ 5 ሺህ 927ቱ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ቀናት ብቻ 79 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊነቱ እየጨመረ እንደሚገኝ ነው ኢንስቲትዩቱ ያስታወቀው፡፡

ወደ ፅኑ ህሙማን ህክምና ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም በየዕለቱ እያሻቀበ እንደሚገኝም ጠቅሷል።

እስከ ትናንትናው ዕለት ብቻ 386 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ ፡፡

በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ከሚገኙት መካከል 61 ህሙማን በመተንፈሻ ማሽን ዕገዛ ላይ እንደሚገኙ ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው፡፡

በቫይረሱም ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ተገልጾ እስካሁን 2 ሺህ 316 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሕብረተሰቡ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ይህንን እውነታ በመገንዘብ የጥንቃቄ መንገዶችን በሚገባ መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡