ባልደራስ እና አብን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የፖለቲካ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።

የሁለቱ ፓርቲ ኃላፊዎች የተመሰረተውን የፖለቲካ ትብብር አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ እንደተናገሩት፤ ፓርቲዎቹ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሰረት በማድረግ ትብብር መስርተዋል።

“በዚሁ መሰረት ፓርቲዎቹ አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወስደዋል” ብለዋል።

ትብብሩ በመጪው ምርጫ የመራጮችን ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለማስቆም የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እንዲፈቱ የጠየቁ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል የንጹሃን ዜጎች ደህንነትና ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ ሲሉም ጠይቀዋል።

የባልደራስ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ በበኩላቸው፣ ትብብሩ የዴሞክራሲ ሂደቱንም ለማጎልበት እንደሚረዳ በመግለጽ፣ የተመሰረተው ትብብር በሕዝቦች ዘንድ ፍትህን ለማስፈን ይረዳል ብለዋል።

የተመሰረተው የፖለቲካ ትብብር ለሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አርአያ ሊሆን የሚችል መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊዎቹ፣ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ፓርቲዎቹ የመሰረቱት ትብብር ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀርቦ የሚፈቀድና የሚመዘገብ ይሆናልም ተብሏል።