ባንኩ የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ለማዘመን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ


መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች “የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር በማዘመን ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት” በሚል ማዕቀፍ በሚተገበር ፕሮጀክት ላይ መክረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ጥምርታ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የታክስ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የሪፎርም ሐሳቦችን የማመንጨት፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ የማሳለጥ እንዲሁም ለታክስ ከፋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶች የጥራት ደረጃዎችን የማሻሻል እርምጃዎችን ያካትታልም ነው የተባለው፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ በየደረጃው በሚገኙ የታክስ ሰብሳቢ አደረጃጀቶች ላይ በወጥነት መተግበር አለበት ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማዎች ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድና የመካከለኛው ዘመን (2016 እስከ 2018) የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ጋር መጣጣም እንዳለበትም በአጽንኦት መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡