ቤንዚን ተጨምሮበት በተለኮሰ ችቦ የተከሰተ የእሳት አደጋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ችቦ ለማቀጣጠል ከመጠን በላይ በተጨመረ ቤንዚን ምክንያት የተከሰተው የእሳት አደጋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ትናንት ከምሽቱ 4 ሰአት ገደማ በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 በዝናብ ምክንያት አልቀጣጠል ያለ ችቦ ላይ ተገቢ ያልሆነና ከመጠን በላይ ቤንዚን በመጨመሩ ምክንያት አደጋው መከሰቱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የተለኮሰው ችቦ ርዝመቱ ከፍ ያለ በመሆኑ እሳቱን በፍጥነት እንዲቀጣጠል አድርጓል፤ ይሄም እሳቱን ለመቆጣጠር ከአካባቢው ማህበረሰብ አቅም በላይ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።
ለኮሚሽኑ በደረሰ ጥቆማ የእሳት አደጋ ጊዜ ሰራተኞች በፍጥነት ወደ ስፍራው በመድረስ እሳቱ ወደ መኖሪያ ቦታዎች ሳይዛመት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አመልክተዋል።
ሰራተኞቹ እሳቱን ለማጥፋት ኬሚካል ፎም መጠቀማቸውንም ጠቁመዋል።
ከተጠቀሰው አደጋ ውጪ የበዓሉ ዋዜማ በአጠቃላይ በሰላም አልፏል ማለት እንደሚቻልና ለዚህም የህብረተሰቡ ድርሻ ወሳኝ የሚባል እንደሆነ ነው ባለሙያው የገለጹት።
ማህበረሰቡ የአዲስ ዓመት በዓልን ሲያከብር ከእሳትና ከኤሌትሪክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።