ብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን ለማስቀረት የተከናወኑ ሥራዎች

መስከረም 11/2014 (ዋልታ) – የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ብሄራዊ  የደህንነት  ስጋቶችን  በማስቀረት  በኩል  ስኬታማ ሥራዎች ማከናወኑን  አስታወቀ፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በ2013 የሥራ ዘመን የማጠቃለያ የዕቅድ አፈጻጻም ላይ ጥልቅ ግምገማ በማድረግና በ2014 የሥራ ዘመን ዕቅድ ዝርዝር ተግባራት ዙሪያ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፈው የበጀት ዓመት ሀገራዊ አንድነትን ለማፍረስ ዒላማ ያደረጉ የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችን በመቀልበስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በተለይ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ  ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን  በማድረግ በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫ ቀንና ከምርጫ ቦኃላ ሂደቱ ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፌደራልና ከክልል የደህንነትና የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ጉልህ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ የ2ኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ የተጣለበትን ተቋማዊ ኃላፊነት በመወጣት  ቁልፍ ሚና ማበርከቱን አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ካለው የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ወሳኝ የመረጃ ስምሪቶችን በማከናወንና አመራር በመሥጠት የተደቀነውን ብሔራዊ የደህንነት ስጋት በማስቀረት በኩልም ተልዕኮውን  ተወጥቷል ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራሉ።

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱን የመፈጸም  አቅም  ለማሳደግ  ባለፈው ዓመት በተለይ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሎጀስቲክስ፣ ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር በኩል በርካታ ሥራዎች በትኩረት ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተመስገን፣ የውስጥና የውጭ ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድም ውጤታማ ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም የተቋሙን አፈጻጻም የሚያሻሽሉ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥራዎች  እንደሚከናወኑ አያይዘው ጠቁመዋል።

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱም የሀገር ህልውናና አንድነትን ለማስጠበቅ ህወሃትን ጨምሮ በሽብርተኞች ላይ መወሰድ ከተጀመረው የተቀናጀ እርምጃም ጋር በተያያዘ ተቋማዊ ተልእኮን የመወጣቱን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ በቀጣይ የሚከናወነው የ3ኛው ዙር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ሌሎች አበይት የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለማስቀረት ከፌደራልና ከክልል የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱን እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል፡፡

በ2014 የበጀት ዓመት አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን በመተንተን የሀገር ብሄራዊ ደህንነትን የሚያረጋግጥ፤ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን ጠንካራ ፕሮፌሽናል ተቋም ለመገንባት የተጀመሩትን ፈርጀ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውንም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ ጠቁሟል።