ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ካቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አደረገ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ተሣትፈው በድምፅ መስጠት ሂደቱ ላይ አቤቱታ ካቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል።

የምክክር መድረኩ በፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን መፍትሔ ለመስጠት ቦርዱ በሚከተለው ሥርዓት ላይ ካለው ጊዜ አንጻር ፓርቲዎቹ ፈጣንና የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል ያሏቸውን የማዳበሪያ ሃሳቦች እንዲያጋሩ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ከቀናት በፊት ፓለቲካ ፓርቲዎቹ አቤቱታዎቻቸውን የሚያቀርቡበትን የመረጃ አቀራረብ ቅደም ተከተል ገምግሞ የትኞቹ ጉዳዮች አቤቱታ የሚቀርብባቸው እንደሆኑ እንዲሁም በምን መንገድ መቅረብ እንዳለባቸው በይፋ መግለጹ ይታወቃል።

አቤቱታዎችን ለማደራጀትና ፓርቲዎቹ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁትን የመፍትሔ ሃሳቦች ሥርዓቱን ተከትሎ አደራጅቶ ለቦርዱ የሚያቀርብ የሕግ ባለሞያዎች ቡድን እንዳቋቋመም ተገልጿል፡፡

ተሣታፊዎቹ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ የፓርቲዎቹን ሃሳብ ለመስማት መድረክ ማዘጋጀቱን፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ያልነበረ ተሞክሮ ነው በማለት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሂደቱን ያግዛል ያሉትን የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦች ማጋራታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ቦርዱ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያመቸው ዘንድ ተመሳሳይ ስታንዳርድ ያለው የአቤቱታ ፎርም በማዘጋጀት እና የፓርቲዎችን አቤቱታ ከሚቀበሉ የህግ ባለሞያዎችን በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።