አምባሳደር ዓለምፀሐይ እና የዩጋንዳው የውሃና አከባቢ ሚኒስትር ውይይት

መስከረም 13/2014 (ዋልታ) በዩጋንዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሰረት ከዩጋንዳ የውሃና አካባቢ ሚኒስትር ሳም ቺፕቶሪስ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው የታላቁ የህዳሴ ግድብ በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት እየተከናወነ መሆኑን፣ አገራችንን አረንጓዴ የማልበስ እቅድ ልምድ ወደ ጎረቤት ሀገራት የማስፋፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ በአገራችን በሰኔ ወር የተደረገውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በቅርቡ መንግስት እንደሚመሰርት፣ የህወሓት አሸባሪ ቡድን መንግስት ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ ባለመቀበል ህፃናትን ወደ ጦርነት እየማገደ እንደሆነ፣ በአማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ ንፁሃን ዜጎችን በግፍ እያጠቃ እና መሰረተ ልማቶችን እያወደመ መሆኑን አምባሳደር ዓለምፀሐይ አብራርተውላቸው፡፡
ሚኒስትር ሳም ቺፕቶሪስ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት እንደሚከታተሉ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንደሆነችና ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳላት፤ ኢትዮጵያ ኃይልን ለማመንጨት የናይልን ወንዝን የመጠቀም መብትን ማንም ሊከለክላት እንደማይችል ገልጸው፣ በተፋሰሱ አገራት መካከል የሚከሰት አለመግባባት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ ለመድረስ በቅን ልቦና መደራደር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አያይዘውም በዓባይ ወንዝ ላይ ያለውን የትብብር አስፈላጊነት አፅንዖት በመስጠት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ የግድቡ መገንባት በተፋሰሱ አገራት የውሃን ፍሰት ከመቆጣጠር ጀምሮ በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር በሚኖረው ጠቀሜታ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን ለመጠበቅ እያደረገች ያለውን ሰፊ እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደሚያደንቁና በኢትዮጵያ በቀን 40 ሚሊዮን የተደረገውን የችግኝ ተካለ ልምድ በመውሰድ በሀገራቸውም መድገም እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!
3