አምባሳደር ዲና ኤችአር 6600 ረቂቅ ህግ ሰላም ለማስፈን የተጀመረውን ውይይት ያላገናዘበ ነው አሉ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) ኤችአር 6600 ረቂቅ ህግ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ሁለንተናዊ ሰላም ለማስፈን የጀመሩትን አገራዊ ውይይት ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ዲና ይህ ማዕቀብ የመጣያ ረቂቅ ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ከፍተኛ ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

በፋይናንስ ረገድ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት እና ባንኮች የምታገኘውን ብድር እና እርዳታ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ የሚያግድ ሲሆን ይህም በአገሪቱ የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዙሪያም ኢትዮጵያን ከየትኛውም የአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽኖች የሚያግድ ሲሆን ይህም በዋናነት በአገሪቱ ላይ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማደናቀፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ረቂቅ ህጉ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቀብ ላይ ያለመ መሆኑም ተነስቷል፡፡

ኤች አር 6600 የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሰላምን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ያለውን እርምጃዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ መግባባትን ለመፍጠር እና ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ያላገናዘበ መሆኑንም አስረተዋል፡፡

ከምንም በላይ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የሚያሰሙትን ድምጽ ወደ ጎን ያደረገ እና ያገለለ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ መንግሥትን በኃይል እና እጅ በመጠምዘዝ ለመጣል የአንድ ወገን ፍላጎትን ያንጸባረቀ ረቂቅ ህግ ሆኖ እንደሚወሰድም ተመላክቷል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን አሸባሪው ትሕነግ በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ በከፈተው ጦርነት ምክኒያት የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰበትን ስቃይ እና ግድያ ረቂቅ ህግ እንዳልተመለከተና በአፋር እና በአማራ ክልሎች አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመውን ግፍ እና በደል በኤችአር 6600 ረቂቅ ላይ አንድም ቦታ ጥፋተኝነቱን የሚገልፅ ጽሑፍ እንዳልተካተተ ተጠቁሟል፡፡

ይልቁንም ኤችአር 6600 ይህ ሽብርተኛ ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልል ሲያደርስ የነበረውን ወረራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዘው ሆኖ እንደተገኘም ተመላክቷል፡፡

ለአንድ ወገን ያደላው ይህ ረቂቅ ህግ የሚፀድቅ ከሆነ ትህነግ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የከፈተውን ጦርነት የሚያባብስ እና አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት እና አጋርነት የሚያበላሽ ነውም ተብሏል፡፡

ለዚህም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከምን ጊዜውም በላይ  ረቂቁን ጠንክረው የሚቃወሙበት ጊዜ መሆኑን በርካቶች እያነሱት ይገኛሉ፡፡

በሜሮን መስፍን