ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ሁለቱ ተቋማት የፈጠራ፣ ምርምርና ስርጸት ድግግሞሽ ለመቀነስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ፣ ሃገራዊ የፈጠራ ሥራን በማዳበር እንዲሁም የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንን መረጃዎቹን በልዩ ሁኔታ የመጠበቅ ሥራዎችን አስተዳደሩ ይሰራል ብለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በኢትዮ የሳይበር ታለንት ማእከል ያሉ የባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችን እና በሌሎች የአስተዳደሩ ባለሙያዎች የሚበለጽጉ የሶፍትዌር እና ሃርድዌር ምርቶችን የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት የማስመዝገብ ሥራ እንሰራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው ለሀገራዊ ፈጠራ መጎልበት በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሥራ እድል ፈጠራ ማደግ እና ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ከኢመደአ ጋር በመተባበር እነዚህን መረጃዎች ደኅነነታቸውን ለማስጠበቅ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
ባለስልጣኑ አቅሙን ለመገንባት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አስተዳደሩ እንደደገፋቸው የገለጹት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢመደአም ከቴክኖሎጂ ድጋፍ ባሻገር የመረጃዎችን ደኅንነት በማረጋገጥ የራሱን ሚና ይጫወታል ማለታቸውን ከኢመድአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።