ለጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ መሰራጨቱ ተገለጸ

ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት ለሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ስር ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያና መድኃኒት መሰራጨቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የሀገሪቷን የጤና ተቋማት የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራር ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገልጸዋል።

ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ የህክምና መሳሪያና የመድኃኒት አቅርቦት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሀገራችን መድኃኒት አምራቾች፣ የህክምና መሳሪያና መድኃኒት አስመጭ ድርጅቶች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ስር ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች መሰራጨታቸውንም ተናግረዋል።

በተለይ በኅልውና ዘመቻ ወቅት በአሸባሪው ሕወሓት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና አግልግሎት እንዲጀምሩ በማድረግ በኩል የተሻለ ስራ ተሰርቷል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራሩን ከማዘመን ጀምሮ ሰፊ ሥራዎች ከፌዴራል ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የሚጠብቁን ቀዳሚ ተግባር ናቸው ብለዋል።

በአማራና በአፋር ክልል 42 ሆስፒታሎችን መልሶ በማደራጀት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑን አመልክተዋል።

በጤና ተቋማት ፈጣን አገልግሎት ለመስጠትና የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ ዘመናዊ የመድሐኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራር ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የመድሐኒት ብክነት፣የአያያዝና የዘመናዊ አሰራር ጉድለት፣ የክምችት ቦታዎችና የህክምና መሳሪያዎች ጥገና ማዕከላት እጥረት በጤና ተቋማት የሚታዩና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት የሆኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ ዓመት ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የህክምና መርጃ መሳሪያዎች በተለይ የኤክስሬይ፣ ራዲዮሎጅና ሌሎች መሳሪያዎች ጥገና እንደተደረገ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።