አሸባሪው ሕወሓት በደቡብ ወሎ ጉዳት ያደረሰባቸው መኖሪያ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ ተጀመረ

ነሐሴ 13/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በደቡብ ወሎ ዞን ወረራ በፈጸመበት ወቅት ጉዳት ያደረሰባቸው ከ2 ሺህ 600 በላይ መኖሪያ ቤቶችን የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የፈጸመው ግፍ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን ገልጸዋል።

ንፁሃንን በግፍ በጅምላ ከመጨፍጨፍ ባለፈ ማኅበራዊ ተቋማትን ጭምር በማውደም እና በመዝረፍ ለሕዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞንም በርካታ ውድመት ቢያደርስም መንግሥት ኅብረተሰቡን፣ የተለያዩ ድርጅቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ከ2 ሺሕ 600 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ ቤቶችን የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸውም መካከል 617 ቤቶች ከነንብረታቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ቀሪዎች እስከ 90 በመቶ የወደሙ ናቸው ብለዋል።

ቤቶችን መንግሥት ባለሃብቶችን፣ ድርጅቶችን እና ኅብረተሰቡን በማስተባበር በ40 ሚሊዮን ብር መልሶ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የቤቶቹ መልሶ ግንባታም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሸባሪው ጉዳት የደረሰባቸው መኖሪያ ቤቶችን በመረዳዳት መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ይመር ናቸው።
ቤታቸው የወደመባቸው ዜጎች በክረምቱ ዝናብ እየተቸገሩ በመሆኑ በፍጥነት ተገንብተው ችግሮቻቸውን ለመፍታት በየደረጃው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአንድ ቤት 56 የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
ለቤት መሥሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ካደረጉ ባለሃብቶች መካከል አቶ ነጋ መሐመድ የወሎ ባለሃብቶችን በማስተባበር ከአንድ ሺሕ 300 በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ሌሎች ተቋማትም መልሰው እንዲቋቋሙ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ዜጎችም በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከመንግሥ ጋር በቅንጅት እንሠራለን የድርሻችንንም እንወጣለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተውለደሬ ወረዳ የ07 ቀበሌ አርሶ አደር ሞሚና አሊ፣ አሸባሪው ሕወሓት የሰው ልጅ የማይፈጽመውን ግፍና መከራ ቢፈጽምብንም በወገኖቻችንና መንግሥት ብርታት መልሰን እየተቋቋምን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የወደመባቸውን ቤታቸውን መንግሥት ድጋፍ ሰጪዎችን አስተባብሮ መልሶ እየገነባላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ለፈጣን መረጃዎች፦