አየር መንገዱ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ ያስገባውን ገቢ በውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን በዶላር፣ በፓውንድና በዩሮ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት አየር መንገዶች በገቡት ውል መሰረት የቲኬት ሽያጭ በአገራት የመገበያያ ገንዘብ ይፈጸማል።

ይህንንም ተከትሎ በአገራት የመገበያያ ገንዘብ በሚካሄድ የቲኬት ሽያጭ የተገኘውን ገቢ ለትኬቱ ባለቤት አየር መንገድ በዶላር፣ በፓውንድ ወይም በዩሮ ተቀይሮ ገቢ እንደሚደረግለት ጠቅሰው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም አየር መንገዱ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ ያስገባውን ገቢ በወቅቱ እየሰበሰበ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ አፍሪካ አገራት ግን አየር መንገዱ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ ቀይሮ በማስረከብ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው 

      

በዚህም አየር መንገዱ ከተለያዩ አፍሪካ አገራት አየር መንገዶች ከትኬት ሽያጭ ያገኘው ከ180 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ እስካሁን ሳይከፈለው መቆየቱ ተገልጿል።

ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀመጫውን ካናዳ ካደረገው ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (አይአታ) ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (አይአታ) ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ በሚቀበልበት ምቹ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያነሱት።

ከዚህ ጎን ለጎንም አየር መንገዱ ከተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።

የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ከአገራት የኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ጠቅሰው በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ አገራት በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ እድገታቸውን አጠናክሮ ማስቀጠልና የውጭ ምንዛሬ አቅማቸውን በዛው ልክ ማጎልበት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በትግበራ ሂደት ላይ ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናም የአፍሪካን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት እውን ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ 134 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን በቅርቡም በአውሮፓና በአፍሪካ ስድስት አዳዲስ መዳረሻዎችን ለመጨመር እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።