የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም የአፍሪካ አገራት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ “ከፍተኛ ቅድሚያ” የሚሰጣቸውን ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት መከተብ እንዳለባቸው አሳሰበ።
ኮቫክስ 90 ሚሊየን ክትባቶችን ወደ አፍሪካ በቅርቡ ማሰራጨት ይጀምራል ያለው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የስርጭት መጠኑም የሚወሰነው አገራት ባላቸው የሕዝብ ብዛት መጠን መሆኑ ተመልክቷል።
ለእያንዳንዱ አገር የሚከፋፈለው ክትባት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ተሰልፈው እየሰሩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚያገኙት ሳይሆን፣ ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካላትንም ለመከተብ ያስችላል ብሏል።
ሁሉም የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ክትባት እንዲያገኙ የሚሰራው ኮቫክስ የተሰኘው ጥምረት ክትባቱን መቼ እንደሚያጓጉዝ እና የትኛው አገር ምን ያህል እና መቼ ያገኛል የሚለውን ዝርዝር አውጥቶ መጨረሱ ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባትን በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ መስጠት መጀመር አለባቸው ብሏል።
በድርጅቱ ከክትባት ጋር በተያያዘ የሚሰሩት ዶ/ር ሪቻርድ ሚሂንጎ ክትባቱ በሚቀጥሉት አንድና ሁለት ሳምንታት መስጠት እንዲጀምር “አገራት የመጀመሪያውን ደረጃ ዝግጁነት ያሟላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ካሉ በኋላ በየካቲት ወር መጨረሻ ክትባቱ መሰጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ይህ ኮቫክስ ለአፍሪካ አገራት የሚሰጠው 90 ሚሊየን ክትባት የመጀመሪያው ዙር ሲሆን፣ እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ድረስ 600 ሚሊየን ያህል ክትባቶች ለአፍሪካ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠብቅ ተገልጿል።
ይህ ክትባት አገራት ካላቸው የሕዝብ ብዛት ውስጥ እስከ 20 በመቶ ድረስ መከተብ ያስችላቸዋል ተብሏል።
በፈረንጆች 2022 እያንዳንዱ አፍሪካዊ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ያገኛል ተብሎ እቅድ መቀመጡንም የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ከኮቫክስ በአቻነት የአፍሪካ ሕብረት የጀመረው ጥረት መኖሩን የተናገረው የዓለም ጤና ድርጅት በእነዚህ ሁለት መንገዶች በሚገኝ ክትባት በ2021 መጨረሻ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱ አፍሪካውያን ክትባቱን ያገኛሉ ተብሎ ታቅዷል።
ይህም በ2022፣ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ክትባቱን ማግኘት ያስችላቸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡