ደንብ በተላለፉ ከ240 በላይ ባጃጆች ላይ እርምጃ ተወሰደ

 

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ላይ የተገኙ ከ240 በላይ ባጃጆች ላይ እርምጃ ወሰደ።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዥን በአንድ ወር ውስጥ ባደረገው ቁጥጥር በተለያዩ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ላይ የተገኙ ከ240 በላይ የሚሆኑ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዥን ከጥር 1 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በክፍለ ከተማው ባደረገው ቁጥጥር ከ30 በላይ የሚሆኑ ባጃጆችን ያለመንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ ተገኝተዋል።

ከ210 በላይ የሚሆኑ ባጃጆች ደግሞ በተለያዩ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች ላይ እንዲሁም ትርፍ በመጫንና የትራፊክ ፖሊስ አባላትን ጥሶ በመሄድ ጥፋት ላይ በመገኘታቸው እንደየጥፋት ደረጃና ደንቡ በሚያዘው መሰረት እስከ 8 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ትራፊክ ጥበቃና ቁጥጥር ዲቪዥን ቲም ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ዮሐንስ መብራቱ እንደተናገሩት፤ በክፍለ ከተማው በርካታ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበትና አብዛኛው አሽከርካሪ በማህበር ተደራጅቶ ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ነገር ግን አንዳንድ ስነ -ምግባር የጎደላቸው አካላት ለትራፊክ ህግና ደንብ ተገዥ ባለመሆን ለመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ መከሰት ምክንያት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በቀጣይ ህግና ደንቡን በማያከብሩት ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚደረግ ምክትል ኢንስፔክተር ዮሐንስ መጠቆማቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመልክቷል።