ኢሬቻ የወንድማማችነትና የአንድነት ተምሳሌት ነው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢሬቻ የወንድማማችነትና የአንድነት ተምሳሌት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤው የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የወርኃ ክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከዘመን ዘመን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ የሚያቀርበው የምስጋና በዓል ነው ብለዋል።

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን በወንዞች ሙላት ተራርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማዶች የውኃው ሙላት ጎድሎላቸው፣ ምድር በአዕዝርት ለምልማና በአበቦች አሸብርቃ፣ እንስሳት ጠግበው ሲቦርቁ ለማየት ላደረሳቸው አምላክ ምስጋና የሚያቀርቡበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ጾታ፣ እድሜ፣ እምነት ሳይገድበው በደስታ፣ በፍቅርና በአብሮነት ከሌሎች ወንድምና እህት ብሄር ብሄረቦች ጋር የሚያከብረው የአደባባይ በዓል ሲሉም አብራርተዋል።

ኢሬቻ ለሕዝብ፣ ለአገር፣ ለእንስሳት፣ ለአራዊት፣ ለወንዝ፣ ለተራራና ለእጽዋት ሰላም መሆንን የሚመኙበት ፤ የሰው ልጆች ጸባቸውን አቁመው እርቅ እንዲያወርዱ፣ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በመቻቻል እንዲኖሩ አምላካቸውን የሚለምኑበትና መልካም ምኞቶታቸውን የሚገልጹበት በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ የይቅርታ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ሲከበር ሕዝቦች በአንድነት ሆነው አምላካቸውን ምህረት የሚጠይቁበት፣ ፈጣሪ ሰላም እንዲያወርድላቸው፣ የተዘራው አዝመራ ፍሬያማ እንዲሆንላቸው፣ እንስሳት እንዲጠግቡ አምላካቸውን አጥብቀው የሚማጸኑበት በዓል ነው ብለዋል -የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው፡፡

ከኢሬቻ በዓል የምንማረው የሚያጋጥሙንን ችግሮችና አለመግባባቶች በወንድማማችነት (በእህትማማችነት) መንፈስ ማስወገድ እንደሚኖርብን ነው፡፡ በመሆኑም ከሚያለያዩን ይልቅ በሚያቀራርቡን እሴቶቻችን ላይ አተኩረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የጀመርነውን የብልጽግና ጎዳና ዳር ለማድረስና የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ እድገቶቻችን የተፋጠነ እንዲሆን በመልካም እሴቶቻችን ላይ በመመሥረት በአንድነትና በአብሮነት መቆም ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በመከባበር፣ በመረዳዳትና በመመካከር ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላችንን አበርክቶ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለብን ገልጸዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።