ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወራት ውስጥ 25.54 ቢሊየን ብር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸምን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተቋሙ በተያዘው በጀት አመት ስትራቴጂካዊ ግቦቹን ለማሳካት መጠነ ሰፊ የለውጥና ማሻሻያ ስራዎች መስራቱን ስራ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ ያስመዘገበው ገቢ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 12.3 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ የአገልግሎት አይነቶቹን በማሳደግ እና ጥራት በማሻሻል በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ስራ አስፈፃሚዋ፣ በስድስት ወራት ውስጥ 80.21 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡
የኩባንያው ደንበኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ላይ የደንበኞች ብዛት 50.7 ሚሊየን መድረሱና ይህም 11.2 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
የደንበኞች አገልግሎት ተጠቃሚነት አይነት 48 በመቶ የድምጽ፣ 309.4 ሺህ የመደበኛ ብሮድባንድ፣ 981 ሺህ የመደበኛ ስልክ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚነት 23.54 ሚሊየን ደርሷልም ተብሏል፡፡ በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትዎርክ ሽፋን 95 በመቶ መድረሱ ተነግሯል፡፡
የተቋሙን ካፒታል ወደ 400 ቢሊየን ብር በማሳደግ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎት ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ወ/ሪት ፍሬህይወት፣ የሞባየል መኒ (mobile money) አገልግሎት ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ እቅዱን ሙሉ በሙሉ እንዳያሳካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሀገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት እና ሌሎችም ተግዳሮት እንደሆነበት አመልክተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የቴሌኮም መቆረጥ ዋንኛ ችግር እንደነበረ የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ፣ በክልሉ የቴሌኮም አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር በርብርብ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
(በመስከረም ቸርነት)