ኢትዮጵያ ከአገራት ጋር ያላት ፖለቲካዊ ግንኙነት እየተሻሻለ በመምጣቱ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል – አምባሳደር መለስ ዓለም

አምባሳደር መለስ ዓለም

ጥቅምት 22/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ከአገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላት ፖለቲካዊ ግንኙነት እየተሻሻለ በመምጣቱ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።

አምባሳደር መለስ ዓለም ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ጋዜጠኞች ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን እና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮ ላይ የውጭ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በሩብ ዓመቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ ትኩረት በማድረግ በ48 የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ መድረኮች ላይ ተሳትፎ መደረጉን አብራርተው ከ600 በላይ ኩባንያዎች የተሳተፉበትን በቻይና ሻንሀይ እና ሻንዱ ከተሞች የተካሄዱ መድረኮችን እና በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ የተካሄዱ ውጤታማ መድረኮችን አንስተዋል።

በመድረኮቹ ላይ የተገኙ ስኬቶች ወደ ተግባር እንዲገቡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀጣይ ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከ53 በላይ የውጭ ባለሀብቶች በአገራችን የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማካሄዳቸውን እና መካከለኛው ምሥራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ እንዲሁም ከአውሮፓ እና አሜሪካ አምስት ኩባንያዎች ከአገራችን ኩባንያዎች ጋር ሽርክና እንዲፈጥሩ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ የቱሪዝም ፍሰትን ከመጨመር አኳም በ31 መድረኮች የአገራችንን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስተዋወቅ 33 አስጎብኝዎች አገራችንን በጉብኝት ማዕቀፋቸው ውስጥ እንዲያስገቡ መደረጋቸውን አንስተዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናው መስሪያ ቤት እና በሚሲዮኖች የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ያብራሩት አምባሳደር መለስ በቀጣይ ሳምንታት ውስጥም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ አቅዳ እየሰራች መሆኑን መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።