ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ


ጥቅምት 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ኅብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለና እስካሁን በነበረው ሂደት ከ18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተሰበሰበ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲጨምር የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በዘንድሮ በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 279 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም በቦንድ ግዢና በስጦታ እንዲሁም በ8100 A አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተሰበሰበ መሆኑን አመላክተዋል።

ለገቢ አሰባሰብ በየክልሎቹ ወጥ የሆነ አደረጃጀት አለመኖሩን እንደ ተግዳሮት ያነሱት ዳይሬክተሩ ሁሉም ክልሎች የሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ በገቢ አሰባሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የግድቡ ግንባታ እየተገባደደ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ አፈፃፀሙ 92 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው