ኢትዮጵያና ሩሲያ በሳይንስና ትምህርት ዘርፍ ትብብራቸውን ላማላቅ ተወያዩ

ኢትዮጵያና ሩሲያ

የካቲት 02/2014 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭገኒይ ተረክሂን ኢትዮጵያና ሩሲያ በሳይንስና ትምህርት ዘርፍ ትብብራቸውን ላማላቅ በሚችሉበት ስልት ላይ ተወያዩ።

ሁለቱ አገራት በሳይንስና ትምህርት ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር ስለሚችሉበትና ያሉ አስቻይ የሕግ ማዕቀፎችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ነው የተወያዩት።

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ በፌስቡክ ገጹ ሚኒስትሩ በሳይንስና ትምህርት ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከወኑ የማሻሻያ ዕቅዶች ለአምባሳደሩ በዝርዝር አብራርተዋል ብሏል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ አያሌ ዜጎች የትምህርት ዕደል በመስጠት ዘርፉን ስትደግፍ መኖሯ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ዛሬ ላይ የልህቀት ማዕከል እየሆነ የመጣው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (የቀድሞው ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት) ለሁለቱ አገራት የትምህርት ዘርፍ ነባርና ጠንካራ ወዳጅነት አንዱ ማሳያ ሆኖም ተንስቷል።

ሚኒስትርና አምባሳደሩ በውይይታቸው ለሁለቱ አገራትና ሕዝቦች የጋራ ጥቅም በትብብር መስራትን ማስቀጠል እንደሚገባ ተስማምተዋልም ተብሏል።