የመንግሥታቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ ያደረጉት ቆይታ የግጭቱን አሳዛኝ መልክ እንዳሳያቸው ገለፁ

የካቲት 02/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ያደረጉትን ቆይታ ተከትሎ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ የግጭቱን አሳዛኝ መልክ ተመልክቻለሁ አሉ።

”ግጭቱ ከወራት በፊት እንደነበረው አይደለም አሁን መጠነኛ መረጋጋት አለው”  ያሉት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ግጭቱ በተከሰተባቸው ቦታዎች የሰብኣዊ እርዳታ አቅርቦት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በቀጣይ አገሪቱ ልታከናውን ያሰበችው የብሔራዊ መግባባት ውይይትም ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም መፍትሄ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

ምክትል ዋና ጸሐፊዋ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በተለይም በአማራ እና አፋር ክልሎች ባደረጉት ጉብኝት አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ያደረሳቸውን የሰብኣዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች እንደዚሁም ቡድኑ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል የቀበረበትን የጅምላ መቃብሮች ጎብኝተዋል።