ኢትዮጵያዊያን በምርጫው ያሳዩት ጨዋነት ለሀገር አንድነትና ሠላም ጅማሮ መሆኑ ተገለጸ

የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያዊያን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ያሳዩት ጨዋነት ለአገራዊ አንድነትና ሠላም ጅማሮ ማሳያ መሆኑን የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ እና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ገለጹ።

የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሀገራዊ ምርጫውና በቀጣይ ሥራዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ኢትዮጵያዊያን መሪያቸውን ለመምረጥ ያሳዩትን ጨዋነትና ትዕግስት አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበሩ መከፋፈሎችና ጥላቻን በማውሳት እርሳቸው ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማምጣት የተሰሩ ስራዎችን ዘርዝረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ በመስጠት ያሳዩት ትዕግስት፣ ጨዋነትና ታጋሽነት ከነበሩት ችግሮች ለመውጣት ለውጥ የሚሹ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።

መራጩ ሕዝብ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያለምንም የጸጥታ ችግር ሥነ-ምግባር በተሞላበት መንገድ ድምጽ ሲሰጥ መዋሉን መታዘባቸውንም ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ

ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካካሄደቻቸው ምርጫዎች ሁለቱን በቅርበት መታዘባቸውን አውስተው፤ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በብዙ መልኩ የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

“በዋናነት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከመሪዎቹ፣ ከልሂቃን ልቆ የታየበት ምርጫ ነው ብዬ ነው የማምነው” ሲሉ መራጩ ሕዝብ የነበረውን ሚና ገልጸዋል።

መራጩ ሕዝብ ዝናብና ጨለማ ሳይበግረው ድምጽ የሰጠበትና ፍጹም ጨዋነት የታየበት ምርጫ መሆኑን በመግለጽ፤ የገዥዎች እንጂ የሕዝብ ታሪክ የሌላትን ኢትዮጵያ ‘የሕዝብ ታሪክ’ ለመጻፍ የሚያነሳሳ ሆኖ እንዳገኙት ነው የተናገሩት።

የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ድምጽ በተሰጠባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ መሪውን ለመምረጥ ያሳየው ጨዋነት በቀጣይ ለአገር ሠላምና እድገት የመጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል።

ዶክተር ብርሃኑ በበኩላቸወ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበው ሕዝብ በእልህና በትዕግስት ድምጽ ለመስጠት ያሳየው ቁርጠኝነት የራሱ የሆነ መልዕክት ያለውና ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም መንግሥት ለሚመሰርተው ፓርቲ ትልቅ የቤት ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ያሳዩት ሥነ-ምግባር መልካም መሆኑን በመጥቀስ፤ ሕዝቡ በድምጽ መስጫው ዕለት ያስቀመጠውን እርሾ በመጠቀም ለቀጣይ እድገት መሥራት እንደሚገባም አክለዋል።

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ሰኔ 14 ቀን 2013 የተካሄደ ሲሆን አጠቃላይ ውጤቱን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።