ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሥራ ዛሬ እንደሚጀመር ተገለጸ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሥራ ዛሬ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቀይ ባህርን በማቋረጥ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሳዑዲ አረቢያን ድንበር ጥሰው ሲገቡ በሳዑዲ ህግ አስከባሪ አካላት ተይዘው እንዲሁም የሳዑዲ የመኖርያና የሥራ ፈቃድ ህግጋትን ተላልፈው በመገኘታቸው በስደተኞች ማቆያ ጣብያዎች ከአንድ አመት በላይ በእስር የቆዩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል።

እነዚህ እስረኞች በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ረዘም ላለ ጊዜ በእስር በመቆየታቸው ሳብያ በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቡና ጫና አሳድሮ ከመቆየቱ ባሻገር የአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሀን መነጋገርያ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል።

በቅርቡ መንግስት እነዚህ እስረኞች በሙሉ ወደ አገር እንዲገቡ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ብዛት ያላቸው በረራዎች ከሳዑዲ ወገን ጋር በመነጋገር የሚመቻቹ ተጠቁሟል።

ይህን ለማሳካት የሁለቱ አገራት መንግስታት ባደረጉት ስምምነት መሰረት ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ ዜጎቻችንን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሂደት ለማሳካት ከኢትዮጵያ ወገን ቀዳሚ ልዑክ ቡድን ተልኮ ከሳዑዲ አረቢያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ጥልቅ ውይይት በማድረግ ዜጎችን የማስመለስ ስራ ተመቻችቷልም የተባለው።

በዚሁ መሰረት ከሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በየቀኑ እስከ ስድስት በሚደርሱ የሳዑዲና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በማቆያ ጣብያዎች የነበሩ ዜጎች የሚመለሱ ይሆናል ተብሏል።

በዛሬው ዕለትም ቁጠራቸው ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ እና በራሳቸው ወጪ ወደአገር ለመግባት ለሚሹ ተመላሾችም በቅርቡ ሁኔታዎች በስፋት እንደሚመቻች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።