ከጋራ ገቢዎች ከ34 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ለክልሎች ተላለፈ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) በ2014 በጀት ዓመት በተቀመጠው የገቢ ማከፋፈያ ቀመር መሠረት ከ34 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ለክልሎች እንዲተላለፍ መደረጉን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ የሚተላለፈው የብር መጠን ከጊዜ ወደጊዜ ከፍተኛ እድገት እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው የጋራ ገቢዎች የማከፋፈያ ቀመር ከመሻሻሉ በፊት በ2012 በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን 179 ሚሊየን 843 ሺሕ 961 ብር፤ ቀመሩ ከተሻሻለ በኋላ ባሉ ተከታታይ ዓመታት በ2013 በጀት ዓመት 22 ቢሊዮን 554 ሚሊየን 130 ሺሕ 784 ብር እንዲሁም በዘንድሮ በጀት ዓመት 34 ቢሊዮን 692 ሚሊዮን 318 ሺሕ 500 ብር እንዲተላለፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የ2014 በጀት ዓመት በ2012 በጀት ዓመት ተላልፎ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የብር 30 ቢሊዮን 512 ሚሊየን 474 ሺሕ 538 እድገት አለው።

በ2013 በጀት ዓመት ተላልፎ ከነበረው ደግሞ የብር 12 ቢሊዮን 138 ሚሊየን 187 ሺሕ 715 ወይም የ53 ነጥብ 82 በመቶ እድገት ማሳየቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የጋራ ገቢዎች የማከፋፈያ ቀመር መሻሻል፣ የገቢ አሰባሰባችን አቅም መጨመርና ክፍፍሉ በተቀመጠው ቀመር መሠረት መሠራቱ ለሚተላለፈው ገቢ ዕድገት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሥራው ስኬት በቅንነትና በቁርጠኝነት የሰሩትን የገቢዎች ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉ አጋር አካላት በራሴና በገቢዎች ሚኒስቴር ስም ምስጋና ይድረሳችሁ ማለታቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል።