ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – ወጋገን ባንክ “በወጋገን ይቆጥቡ፣ በወጋገን ይሸለሙ ” በሚል ስያሜ ላካሄደው የሎተሪ ዕጣ መርሃ-ግብር አሸናፊዎች ሽልማታቸውን አስረከበ፡፡
ባንኩ ለዋልታ በላከው መግለጫ ከጥቅምት 1 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ “በወጋገን ይቆጥቡ፤ በወጋገን ይሸለሙ” በሚል ስያሜ ሲያካሂድ ለቆየው የቁጠባ ማበረታቻ መርሀግብር የሎተሪ ዕጣ አሸናፊዎች ሽልማቶቻቸውን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እና ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት እንዲሁም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካዮች በተገኙበት በይፋ አስረክቧል፡፡
ባንኩ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በይፋ በወጣው ዕጣ መሰረት፡-
1ኛ ዕጣ አንድ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል
2ኛ ዕጣ ሁለት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች
3ኛ ዕጣ 20 የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች
4ኛ ዕጣ 30 ባለ 32 ኢንች ኤል ኢዲ ቴሌቪዥኖች እና
5ኛ ዕጣ 40 ስማርት ሞባይል ስልኮችን ለዕድለኞች አስረክቧል፡፡
አሸናፊዎቹ በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ባሉት አሥሩም የወጋገን ባንክ ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች ሥር የሚገኙ ቅርንጫፎች ደንበኞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ብርቱካን ገብረእግዚ እንደገለፁት ሽልማቱ የባንኩን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ትስስር የበለጠ ከማጎልበት እና ተጨማሪ ደንበኞችን ከመሳብ አንፃርም የራሱን ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የባንኩን የቁጠባ መጠን ከፍ በማድረግ እና የገበያ ድርሻውን ከማሳደግ ብሎም ባንኩ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያቀርበውን ብድር ከመጨመር አንጻር አበረታች አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡