ወጣቶችና ሴቶች በዘመቻው የተጠናከረ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸው ተጠቆመ

ጥቅምት 11/2014 (ዋልታ) የሀገር ማዳን ዘመቻውን ለማሳካት አባሎቻቸው የተጠናከረ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የአማራ ክልል ወጣቶችና ሴቶች ማህበራት አስታወቁ።

የማህበራቱ ሊቃነ መናብርት ለኢዜአ እንደተናገሩት የማህበራቱ አባላት አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ተሳትፏቸውን እያጠናከሩ ነው።

የወጣት ማህበሩ ሊቀ መንበር ወጣት አባይነህ ጌጡ አባላቱ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ የህይወት መስዋትነት በመክፈል ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም ትጥቅና ስንቅ በአግባቡ እንዲቀርብ በማድረግና ሃብት በማሰባሰብ  ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን አስታውቋል።

“ኢትዮጵያ እንደ አገር፤ አማራ እንደ ሕዝብ  የተረጋጋ  ኑሮ የሚኖረው  አሸባሪው  ቡድን ወደ መጣበት እንዲመለስ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ባለበት እንዲቀበር በማድረግ ነው” ብሏል።

የአማራ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ትብለጥ መንገሻ የአሸባሪው ቡድን እስካልጠፋ ድረስ ኢትዮጵያ እንደ አገር ስላም እንደማትሆን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች የአሸባሪውን  ቡድን እኩይ  ዓላማ  ለማክሸፍ  የትጥቅ ትግሉን አየተቀላቀሉ  መሆናቸውን ተናግረዋል።