ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡባዊውን ክፍለ ዓለም ፍላጎት የሚያስተናግድ እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው – ደመቀ መኮንን

መስከረም 5/2016 (አዲስ ዋልታ) ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡባዊውን ክፍለ ዓለምን ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

በኩባ ሀቫና ከተማ እየተካሄደ ባለው የቡድን 77 እና ቻይና የመሪዎችና የመንግስታት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር በተናጠል የሚጣሉ ማዕቀቦችና ኃይልን መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ እርምጃዎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ልማት ለውጦችን ያስተጓጉላሉ ብለዋል።

በደቡብ-ደቡብ የትብብር መድረክ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ ፈጠራን ለማሳደግና ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ወሳኝ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እየተገበረች ባለው የዲጂታል ስትራቴጂ ሰፊውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር ራዕይ ሰንቃ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የቡድን 77 እና ቻይና የመሪዎችና የመንግስታት ጉባኤ በዛሬው ውሎው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳቦችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ እና ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ኢንገር አንደርሰን ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።