የህንድ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 24/2015 (ዋልታ) የህንድ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ለማድረግ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ከሆኑት ሽሪ ሮበርት ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈፃሚው በውይይታቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የህንድ ባለሃብቶች ኢንቨስት በማድረግ የሁለቱን አገራት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነት ከማጠናከር ባለፈ በስራ እድል ፈጠራና በባህል ትስስር ዘርፍ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በርካታ የህንድ ባለሃብቶች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማድረግ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት በበኩላቸው የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታዎች ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን በመፍጠር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ባለሃብቶች ገብተው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

የህንድ ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው በርካታ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።