ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – የኬንያና ኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ግንኙነት መጠናከር ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ትብብር መጠናከርና መስፋፋት እንዲሁም በዲፕሎማሲ ግንኙነቱም ላይ ጉልኽ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ልዑክ ሐይማኖት ለሠላም እና አብሮነት መጠናከር ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ የሥራ ጉብኝት በኬንያ ናይሮቢ እያካሄደ ይገኛል።
ልዑኩ ከኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ከአፍሪካ የሃይማኖት መሪዎች ካውንስልና ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላትና በኬንያ ከኢትዮጵያ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ወይይት ማድረጉን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እና የኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤዎች በቀጣይ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች በመለየት ትብብራቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ የተወያዩ ሲሆን በቀጣይ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እንደሚሰሩ በውይይቱ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በሌላ መልኩ የጉባኤው ጸሐፊ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ እየገነባች ያለውን የሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ እና ከእውነት ጎን በመቆም ላሳየችው ቁርጠኝነት እና ለሰጠችው ድጋፍ በጉባኤው ሥም አመሥግነዋል።
የኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ ቢሾብ ጆሰፍ ማታው “የሁለቱ የሃይማኖት ተቋማት ግንኙነት መጠናከር ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ትብብር መጠናከርና መስፋፋት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል” ብለዋል።
በሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይም ወሳኝ ሚና ይጫወታል በማለት ገልጸዋል።
የአባይን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ በራስዋ ሀብት የመልማት ፍላጎት ትክክለኛ እና ተገቢ መሆኑን ገልጸው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በናይሮቢ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቅርንጫፍ ለመመስረት አደራጅ ኮሚቴ መሰየሙም ተነግሯል፡፡