የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ግብፅ ሳትቀበለው ቀርታለች

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ስብሰባ ላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ ሰነዱን ሳትቀበለው ቀርታለች።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነመረብ ስብሰባ አካሂደዋል።

ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምከር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በማተኮር ምክክር ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደምትመለከተው እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን ገልፃለች፡፡

የሱዳን ወገን በበኩሉ ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው እና በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ ቢጋራ በማጽደቅ ድርድሩን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

የግብጽ ወገን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡

የሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት ቢሆንም፣ ወደፊት በዓባይ ተፋሰስ ላይ በሚገነቡ የውሃ ልማት ሥራዎች ጋር የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሃሳብ ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍጆታ የሌለው የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደመሆኑ በግድቡ ላይ የሚደረሰው ስምምነት ይህንኑ ከግምት ያስገባ እና የተሟላ የውሃ ስምምነት በሌለበት እና ኢፍትሃዊ አጠቃቀም በሰፈነበት ተፋሰስ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን ኢትዮጵያ አትፈቅድም::

ይህን መሰረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ አሞላል እና ዓመታዊ አስተደዳር የሚመለከተውን ደንብ በጋራ ስምምነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት፡፡

በዚህም መሰረት የስምምነት አማራጮችን ለግብጽ እና ሱዳን ወገን ያቀረበች ሲሆን፣ የሃገራቱ ምላሽ ቀና እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡

በቀጣይ የሃገራቱ ባለሙያዎች በውሃ ሚኒስትሮች አመራር ስር ስብሰባቸውን በመቀጠል ስምምነት የተደረሰባቸውን እና የልዩነት ሃሳቦችን በመለየት በቀጣይ እሁድ ጥር 01 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው የስድስት ሚኒስትሮች ስብሰባ ውጤቱን ያቀርባሉ፡፡

አዲስ አበባ (ታህሳስ 25 ቀን 2013)