የመራጮች ምዝገባ መራዘም

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ድምፅ ለሚሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ሲደረግ የነበረው የመራጮች ምዝገባ እስከ መስከረም 2/2014 ዓ.ም መራዘሙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

በሐረሪ ፣ ሶማሌ  የተወሰኑ ምርጫ ክልሎች እና ደቡብ ክልል ምእራብ ኦሞ ዞን የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ጳጉሜ 05 ቀን እንደሚጠናቀቅ ያስታወሰው ምርጫ ቦርድ፣ በተለያዩ ቦታዎች ለመመዝገብ ፈልገው እድሉን ያላገኙ ዜጎችን ለማካተት ሲባል በተጨማሪነት ምዝገባው መስከረም 02 ቀን 2014 ዓ.ም እሁድ እንዲከናወን መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመራጮች ትምህርት ሰጪዎች እና ሚዲያዎች ዜጎች ተጨማሪውን አንድ ቀን ተጠቅመው እንዲመዘገቡ እንዲያበረታቱ ቦርዱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ጠይቋል፡፡