የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

ሚያዝያ 10/2015 (ዋልታ) የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ‘ሩስሃይድሮ’ (RusHydro) በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች ከሩስሃይድሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል የማምረት አቅም ቢኖርም የኢነርጂ አቅርቦቱ ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢነርጂ አቅርቦቱን ለማሳደግ እና በቀጣናው የተጀመረውን የኃይል ትስስር ለማስፋፋት ኢነርጂ የማምረት፣ የማሰራጨት እና የማስተላለፍ አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የኢነርጂ ፍላጎት እያደገ መሄድ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ኢነርጂ ማምረት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን እና ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሩስሃይድሮ የሥራ ኃላፊዎች ለረጅም ጊዜ የቆየ የኃይል ማምረት እና የማሰራጨት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኃይል ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ከውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ 2004 የተቋቋመው ሩስሃይድሮ በሩሲያ ከሚገኙ ግዙፍ የኤሌትሪክ ኃይል ኩባንያዎች አንዱ እንደሆነም ተመላክቷል።