ኤጀንሲው 27 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለተመራቂ ሥራ አጥ ወጣቶች አበረከተ

ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች

ሚያዝያ 10/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ የዘርፉን ባለሃብቶች በማስተባበር የገዛቸውን 27 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ለተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶች አበረከተ።

ኤጀንሲው ከአሽከርካሪ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመተባበር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 840 ተማሪዎችን በነፃ የአሽከርካሪነት ሙያ በማሰልጠን አስመርቋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጀማል ከድር እንደገለጹት ኤጀንሲው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ከማሳለጥ ጎን ለጎን ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች የሥራ ዕድል አግኝተው ጥሪት የሚያፈሩበትን ፕሮግራም በመቅረጽ እየሠራ ይገኛል።

በዚህም ከአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመተባበር 840 የሚሆኑ ተመራቂዎችን በነፃ አሰልጥኖ የአሽከርካሪ ሙያ ፍቃድ እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።

በዚህ ነፃ የስልጠና መርሐ-ግብር ሰልጥነው የአሽከርካሪነት ሙያ ፍቃድ ካገኙት ውስጥ 540 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኤጀንሲው የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማቱን በማስተባበር ከ9.2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 27 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ በመግዛት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 54 ሥራ አጥ ወጣቶች ማበርከቱም ተገልጿል።