ግንቦት 11/2013 (ዋልታ) – በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሽብር ጥቃት ለመከላከል ለሁለት ቀን በተደረገ አሰሳ ስምንት የሸኔ አባላት መደምሰሳቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መከላከል ኃላፊ ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፋየ ለኢዜአ እንደገለጹት እርምጃው የተወሰደው በሁለት ወረዳዎች ጥቃት ለመፈጸም በእንቅሰቃሴ ላይ በነበሩ የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን አባላት ላይ ነው፡፡
በዞኑ ጎሮዶላ ወረዳ ከትላንት በስቲያ በየገጠሩ በተደረገ አሰሳ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ አምስት የጥፋት ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በዞኑ ሊበን ወረዳ ትላንት ጧት በተወሰደ እርምጃ የሽብር ተግባር ለመፈጸም የተሰማሩ ሶስት የጥፋት ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንም አመልክተዋል፡፡
ከመካከላቸው እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አንድ የጥፋት ቡድኑ አባል ከአራት ክላንሽኮቭ ጠብመንጃ ጋር በቁጥጥር ስር እንደዋለ የጠቆሙት ዋና ሳጂን ጉተማ፣ በአዶላ ከተማ በህዝብ ጥቆማ በህገወጥ መንገድ ክላንሽኮቭ ጠብመንጃ የያዘ አንድ ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
“በጥፋት ቡድኑ አባላት በየአካባቢው ሊደርስ የሚችለውን የሽብር ጥቃት ለመከላከል በዞኑ የፀጥታ አካላት እየተደረገ ያለው የአሰሳ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ብለዋል፡፡
የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ የሽብር ጥቃትን ለመከላከል የዞኑ ህዝብ ድርሻ፣ ትብብርና ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ሳጂን ጉተማ አስታውቀዋል፡፡